Ethiopian Orthodox Tewahedo Church - የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

መዝሙር

ስብከት

ምስለ ስዕል

ቅድስት ሀና

YouTube

COVID-19

ትንሣኤ

ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵ 4:13
I can do every thing through Christ which strengthens me. Phil 4:13

 

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
እንኳን በደኅና መጡ !

ጾመ ነቢያት/የነቢያት ጾም/የገና ጾም 

ጾመ ነቢያት በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ በዓለ ልደት ዋዜማ ድረስ የሚጾም ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንደኛው ጾም ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ ስለ መልበሱ ወደ ግብጽ ስለ መሰደዱ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ ለሰው ልጆች ድኅነት ልዩ ልዩ መከራን ስለ መቀበሉ ስለ መሰቀሉ ስለ ሞቱ ትንሣኤው ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ትንቢት ተናግረዋል ትንቢቱ ደርሶ ተፈጽሞ ለመመልከትም ‹‹አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ ኃይልህን አንሣ እጅህን ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው የሚኾንበትን ጊዜ በቀናት በሳምንታት በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡

ይህ ጾም የእግዚአብሔርን ሰው መኾን ሲጠባበቁ የኖሩት የነቢያት ትንቢትና ጸሎት በጌታችን መወለድ ፍጻሜ ያገኘበት ወቅት በመኾኑ ‹‹ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)›እየተባለ ይጠራል፡፡ ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ ስለ ተፈጸመበትም ‹‹ጾመ አዳም (የአዳም ጾም)›› ይባላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሰው መኾን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመኾኑም ‹‹ጾመ ስብከት (የስብከት ጾም)›› የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑ ደግሞ ‹‹ጾመ ልደት (የልደት ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ እንደዚሁም ‹‹ጾመ ሐዋርያት›› ይባላል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›› በማለት ነቢያት የጾሙትን ከልደተ ክርሰቶስ በፊት ያለውን ጾም ጾመዋልና፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ይህ ጾም ‹‹ጾመ ፊልጶስ (የፊልጶስ ጾም)›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያና አውራጃዋ ዅሉ እየተዘዋወረ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ስለ ተሰወረባቸው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ሱባዔ ይዘው በጾም በጸሎት ተወስነው በለመኑት ጊዜ እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀብሎ በ፫ኛው ቀን መልሶላቸው ሥጋውን (አስከሬኑን) በክብር አሳርፈውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ ጌታችን ልደት ድረስ ጾመዋል፡፡ ስለዚህም ጾመ ነቢያት ‹‹ጾመ ፊልጶስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ወልደ አምላክ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደምትፀንሰው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ካበሠራት በኋላ እመቤታችን ‹‹ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ?›› በማለት ጌታችንን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማዋለችና ይህ ጾም ‹‹ጾመ ማርያም›› በመባልም ይታወቃል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሥርዐት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት የሐዋርያት የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ዅላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡

ምንጭ- ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው አንቀጽ ፲፭፡፡

ጾምና ምጽዋት ዲያቆን ቃኘው ወልዴ ገጽ ፵፯ -፶፡፡

 

የነቢያት ጾም/ጾመ ነቢያት/የገና ጾም : አስተምህሮ ስብከት ብርሃንና ኖላዊ

ጾመ ነቢያት (የገና ጾምከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ሲሆንጾመ ነቢያትየተባለበት ምክንያት ነቢያት ስለጾሙት ነው፡፡ነቢያት የጾሙት ስለምንድን ነው?”  ቢሉ ለአዳም የተሰጠውንአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁየሚለውን የተስፋ ቃል በማሰብ ከሰማየ ሰማያት ይወርዳል ከድንግል ማርያም ይወለዳል በሞቱም ሞት የተፈረደበትን የሰው ልጅ ነፃ ያወጣዋል ብለው ነው፡፡ይህንን ጾም የትኞቹ ነቢያት ናቸው የጾሙት?” ቢሉ ሊቀ ነቢያት ሙሴ 40 ቀን ጾሟል (ዘፀ 3427) ነቢዩ ኤልያስም 40 ቀን ጾሟል (1 ነገ 191)፡፡ በተጨማሪም በተለያየ ዘመን የነበሩት ነቢዩ ዕዝራ ነቢዩ ነህምያ ነቢዩ ዳንኤል እንዲሁም ክቡር ዳዊት ጾመዋል፡፡

ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ከጾሙ እኛ እርሱ ወርዶ ተወልዶ ተሰቅሎ ካዳነን በኋላ ያለን የሐዲስ ኪዳን ክርስትያኖች ስለምን የነቢያትን ጾም እንጾማለን?” ቢሉ እኛ የነቢያትን ጾም የምንጾመው እንደቀደሙት ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያልን ሳይሆን የቀደሙት ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያሉ የጾሙትን በማሰብ በመጾማችን ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እንድናገኝበት ነው፡፡ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)  ከኅዳር 15 ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 28 ቀን (በዘመነ ዮሐንስ እስከ ታኅሳስ 27 ቀንድረስ 44 ቀናት (በዘመነ ዮሐንስ 43 ቀናትይጾማል፡፡ ከእነዚህም መካከል 40 ቀናት ጾመ ነቢያት 3 ቀናት ጾመ አብርሃም ሶርያዊ ሲሆኑ የቀረው 1 ቀን ደግሞ የገሃድ ጾም ነው (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 565 567)፡፡ ጾመ ነቢያትን ከኅዳር 15 ጀምሮ ሳይጾሙ የልደትን ዋዜማ ብቻ መጾም የቤተክርስቲያን ሥርዓት አይደለም፡፡

የነቢያት ጾም ስያሜዎች

እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ ስለ መልበሱ ወደ ግብጽ ስለ መሰደዱ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ ለሰው ልጆች ድኅነት ልዩ ልዩ መከራን ስለ መቀበሉ ስለ መሰቀሉ ስለ ሞቱ ትንሣኤው ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ትንቢት ተናግረዋል ትንቢቱ ደርሶ ተፈጽሞ ለመመልከትምአንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ ኃይልህን አንሣ እጅህን ላክእያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው የሚኾንበትን ጊዜ በቀናት በሳምንታት በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ ይህ ጾም-

  1. የእግዚአብሔርን ሰው መኾን ሲጠባበቁ የኖሩት የነቢያት ትንቢትና ጸሎት በጌታችን መወለድ ፍጻሜ ያገኘበት ወቅት በመኾኑ ‹‹ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)›እየተባለ ይጠራል፡፡
  2. ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ ስለ ተፈጸመበትም ‹‹ጾመ አዳም (የአዳም ጾም)›ይባላል፡፡
  3. ስለ እግዚአብሔር ሰው መኾን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመኾኑም ‹‹ጾመ ስብከት (የስብከት ጾም)›ይባላል፡፡
  4. የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑ ደግሞ ‹‹ጾመ ልደት (የልደት ጾም)በመባል ይታወቃል፡፡
  5. እንደዚሁም ‹‹ጾመ ሐዋርያት›› ይባላል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›በማለት ነቢያት የጾሙትን ከልደተ ክርሰቶስ በፊት ያለውን ጾም ጾመዋልና፡፡
  6. በተመሳሳይ መልኩ ይህ ጾም ‹‹ጾመ ፊልጶስ (የፊልጶስ ጾም)›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያና አውራጃዋ ዅሉ እየተዘዋወረ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ስለ ተሰወረባቸው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ሱባዔ ይዘው በጾም በጸሎት ተወስነው በለመኑት ጊዜ እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀብሎ በ፫ኛው ቀን መልሶላቸው ሥጋውን (አስከሬኑን) በክብር አሳርፈውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ ጌታችን ልደት ድረስ ጾመዋል፡፡ ስለዚህም ጾመ ነቢያት ‹‹ጾመ ፊልጶስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡
  7. ከዚሁ ዅሉ ጋርም ወልደ አምላክ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደምትፀንሰው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ካበሠራት በኋላ እመቤታችን ‹‹ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ?›በማለት ጌታችንን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማዋለችና ይህ ጾም ‹‹ጾመ ማርያም›› በመባልም ይታወቃል፡፡

አስተምህሮ (አስተምሕሮ)

ወቅቱ/ጊዜው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዘመን አከፋፈል መሠረት ከኅዳር 6 ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 7 ወይም 13 ቀን ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምሕሮ (አስተምህሮ) ይባላል፡፡

አስተምህሮ ቃሉ በሃሌታው” (“አስተምህሮተብሎ) ሲጻፍ የቃለ እግዚአብሔር ማስተማሪያ (የትምህርተ ወንጌል) ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉምመሀረአስተማረ ለመምህር ሰጠ  መራ አሳየ መከረ አለመደወይምተምህረተማረ ለመደየሚለው የግእዝ ግስ ሲሆን ይኸውም የእግዚአብሔር ቸርነቱ ርኅራኄው ትዕግሥቱና የማዳን ሥራው በቤተክርስቲያን በስፋት የሚሰበክበት ጊዜ ነው፡፡

አስተምሕሮ ቃሉ በሐመሩ” (“አስተምሕሮተብሎ) ሲጻፍ ደግሞ የምሕረት የይቅርታ ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉምመሐረይቅር አለ ዕዳ በደልን ተወወይምአምሐረአስማረ ይቅር አሰኘ አራራ አሳዘነየሚለው የግእዝ ግስ ነው፡፡ ዘመነ አስተምሕሮ ስለ እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ እርሱ በደላችንን ሁሉ ይቅር እንደሚለን እኛ ምእመናንም እርስ በእርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡

ዘመነ አስተምህ()ሮ፡ ዘመነ አስተምሕሮ ስለ እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ እርሱ በደላችንን ሁሉ ይቅር እንደሚለን እኛ ምእመናንም እርስ በእርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ዘመነ አስተምሕሮ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት ምእመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡

በዘመነ አስተምሕሮ የሚገኙ ሰንበታት በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት እንደተቀመጠው በዘመነ አስተምሕሮ ውስጥ የሚገኙ ሰንበታት (እሑዶች) አስተምሕሮ (ኢተዘኪሮ) ቅድስት (ሎቱ ስብሐት) ምኵራብ (አምላክ ፍጹም በሕላዌሁ) መጻጉዕ (ይቤሉ እስራኤል) እና ደብረ ዘይት (ሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ እረፍተ) ተብለው ይጠራሉ፡፡ ሳምንታቱን በዚህ መልክ የከፋፈለውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው (ድጓ ዘአስተምህሮ)፡፡ ከመጀመሪያው ሳምንት (ከአስተምሕሮ) በቀር የአራቱ እሑዶቹ ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡

የሰንበታቱ ስያሜ ከዐቢይ ጾም ጋር ተመሳሳይ ነውንየዘመነ አስተምህሮ ሰንበታት (እሑዶች) ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ስያሜ ጋር ተመሳሳይ ይሁን እንጂ በእነዚህ ሳምንታት ሌሊት የሚዘመሩ መዝሙራት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትና የሚቀርቡ ትምህርቶች ግን በይዘትና በምሥጢር ይለያያሉ፡፡ ትምህርቶቹ በምስጢር ይለያያሉ ስንልም በዚህ ወቅት የሚነገረው ምሥጢርና ይዘት በወቅቱ ላይ የሚያተኩር መሆኑን ለመግለጽ ነው እንጂ በየትኛውም ጊዜ በቤተክርስቲያናችን የሚቀርበው ትምህርት አንዱ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው

1.      ዘመነ ስብከት

በነቢያት ጾም ውስጥ ከታህሳስ 7 እስከ ታህሳስ 26 ቀን ያለው ዘመን ዘመነ ስብከት ይባላል፡፡ ዘመነ ስብከት የተባለበት ምክንያትም ነቢያት የጌታን በሥጋ መምጣት አምልተውና አስፍተው በትንቢትና በትምህርት መስበካቸውን ቤተክርስቲያን እያሰበች ሰውን ለማዳን ወደ ምድር የመጣውን አምላክ የምትሰብክበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡

ስብከትየዘመነ ስብከት የመጀመሪያው ሰንበት (እሑድ) ‹‹ስብከት›› ይባላል፡፡ በዚህ ሰንበት በኦሪተ ሙሴ በነቢያትና በመዝሙራት አስቀድሞ ስለክርስቶስ ሥጋን ተዋሕዶ ሰው መሆን ትንቢት ተነግሮ ምሳሌ ተመስሎ ሱባዔ ተቆጥሮ እንደነበር ይነገራል ይሰበካልም፡፡ ስለዚህ ነቢያቱ አስቀድመው መምጣቱን ሰብከው ስለነበር ያንን ለማሰብ ይህ ሰንበት ‹‹ስብከት›› ተባለ፡፡ ስብከት ማለት ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ትምህርት ማለት ሲሆን በዚህ ሳምንት ከልደተ አብርሃም እስከ ልደተ ዳዊት ባለው ትውልድ ወስጥ ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን የተሰበከው ስብከት ይታሰባል፡፡

የነቢያት ስብከትበስብከት ሰንበት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሴ በሕግ ነቢያትም በትንቢት እንደጻፉለት የሚናገረው ወንጌል ይነበባል (ዮሐ 144) ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም ‹‹እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም›› (መዝ 1437) በማለት ስለክርስቶስ ማዳን በትንቢት መነጽር ተመልክቶ የዘመረው የመዝሙር ክፍል እንዲሁ ይሰበካል፡፡ ከዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም ‹‹ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ›› (ኢሳ 641) ብሎ ስለክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረድ ከድንግል ማርያምም መወለድ የተናገረውን ትንቢት ቤተክርስቲያን ትሰብካለች፡፡

የቤተክርስቲያናችን ስብከትብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እኛስ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን (2 ቆሮ 45) እንዳለው ቤተክርስቲያን በተለይ በዘመነ ስብከት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የሰጠውንና የፈጸመውን የማዳን ተስፋ ትሰብካለች፡፡ ቅዱስ ያሬድም በመዝሙሩ ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለንእንዳለ  ቤተክርስቲያናችን መቼም ቢሆን መቼ በጊዜውም አለጊዜውም ሲሞላም ሲያጎድልም ስለ ኃጢአታችን የሞተውንና አምላክ ወልደ አምላክ  የሆነውን ክርስቶስን ትሰብካለች

2.      ብርሀን

የዘመነ ስብከት ሁለተኛው ሰንበት ‹‹ብርሀን›› ይባላል፡፡ ነቢያት የነፍሳችን ብርሀን ይወለዳል ብለው ስለመስበካቸው እውነተኛ ብርሀን ይመጣል ብለው ሰለማስተማራቸው የሚታሰብበት ሲሆን በዚሁ ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ብርሀን መሆኑ ይሰበካል ይዘመራልም፡፡ ከዚሁ ጋር ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ መከራ ነፍስ የጸናበት የሰው ልጅ ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ነቢያት ያሉበትን ያን ዘመን ጨለማ ብለው በመግለጥ የነፍሳችን ብርሀን ይወለዳል እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለመስበካቸው የሚታሰብበት ቀን/ሳምንት/ ነው በዚህ ሳምንት ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን የነበረው 14 ትውልድ ይታሰብበታል፡፡

የነቢያት ጸሎትነቢያት የአምላክን ማዳን ከጠበቁባቸውና ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን ወደ ዓለም እንዲመጣብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ” (መዝ 423) እንዲህ ብሎ ይጸልይ ነበረ  ይህም ብርሃን ጽድቅ እውነት የሆነውን ልጅህን (ወልድንላክልን እርሱ መርቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባን ዘንድ ማለት ነው (ኢሳ 49)፡፡

እውነተኛው ብርሀንወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም መጣ›› ብሎ እንደመሰከረው እውነተኛ ብርሀን ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሀንነት የሚሰበክበት ሰንበት ነው›› (ዮሐ 11-11) ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም›› (ዮሐ 8:12) ብሎ እንዳስተማረው በዚህ ሰንበት ስለ እርሱ ብርሀንነትና ክርስቲያኖችም እርሱን ብርሀናቸው እንዲያደርጉት ይሰበካል፡፡

የሕይወታችን ብርሀንበዚህ ዕለት ‹‹ከብርሀን የተገኘ ብርሀን›› እንዲሁም ‹‹የማይነገር ብርሃን›› የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን መሆኑ ይሰበካል፡፡ ‹‹ብርሃን ወደ ዓለም መጣ›› እየተባለ በቅዱስ ያሬድ መዝሙር ይመሰገናል እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን ቅዱስ ኤፍሬምም በሰኞ ውዳሴ ማርያም እንዳሰተማረን ‹‹በዚህ አለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሀን ስለሰው ፍቅር ወደ አለም የመጣህ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተቱ አድነኽዋልና፡፡ ሔዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነጻ አድርገኃታልና የምንወለድበትን መንፈስ ሰጠኽን ከመላዕክት ጋርም አመሰገንህ›› በማለት የሕይወታችን ብርሀን የሆነውን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመሰግናለን፡፡

3.      ኖላዊ

የዘመነ ስብከት ሦስተኛው ሰንበት ‹‹ኖላዊ›› ይባላል፡፡ ኖላዊ ማለት ‹‹እረኛ›› ወይም ‹‹ጠባቂ›› ማለት ሲሆን በዚህ ዕለት ነቢያት የእግዚአብሔር ልጅ እውነተኛ ጠባቂ ሆኖ ይገለጣል ብለው መተንበያቸው እና ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ጠባቂ መሆኑ ቤተክርስቲያናችን እያሰበች የምትዘምርበት የምትቀድስበት የምታመሰግንበት ዕለት ነው፡፡

የእስራኤል ጠባቂነቢያት ራሳቸውንና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው በጎች በመቁጠር ስለ እውነተኛው እረኛ መምጣት ትንቢት ተናግረዋል በዚህ ሰንበት ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው አሥራ አራት ትውልድ የነበረው ሰንበት ይታሰባል በዚህ ሰንበት ቤተክርስቲያናችን እረኛ የሌለው በግ ተኵላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ምክንያት ከትጉህ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም ሰብሳቢና የሚያሰማራ ጠባቂ እንዲኖረው ነቢያት ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ (መዝ 791) በማለት ይማፀኑ እንደነበር ታስተምራለች

ቸር ጠባቂየትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል›› ዮሐ 1011 በማለት እውነተኛ አእረኛ እርሱ መሆኑን መልስ ሰጥቷል ስለራሱም ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ›› ዮሐ 1015 በማለት አስተምሯል፡፡

በልበ አምላክ ክቡር ዳዊትምእግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል መዝ (221) ተብሎ እንደተጻፈ በዚህ የጾም ወቅት አቤቱ ብርሀንህንና ጽድቅህን ላክ ቸሩ እረኛችን ሆይ ተቅበዝብዘናልና እባክህ አስበን የቀዘቀዘው ፍቅራችንን መልስልን አንተ እውነተኛ ሰላምህን ስጠን እያልን ምንም ወደ ማያሳጣን ወደ እውነተኛው እረኛችን ወደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በንስሐ ልንመለስ ይገባል

ከተኩላዎች ተጠበቁ:  ለክርስቲያኖች ሁሉ የታመነ ጠባቂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹በጎቼን ጠብቅ›› ብሎ ቅዱስ በጴጥሮስ በኩል አደራ የተሰጣቸው ካህናተ ቤተክርስቲያን የመንጋው ጠባቂ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሐሰተኛ በበዛበት ዘመን እውነተኞቹን እረኞች ከተኩላዎቹ መለየት ያስፈልጋል፡፡ የምንለያቸውም በፍሬያቸው ነው (ማቴ 715) መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ እንዲያፈራ መልካም እረኛም ለበጎቹ መልካምን ያደርጋል፡፡ ተኩላ ግን በጎችን ሊጠብቅ ሳይሆን ሊነጥቅ እንደሚመጣ ሐሰተኞች እረኞችም ምዕመናንን ሊጠብቋቸው ሳይሆን ሊነጥቋቸው ይፍጨረጨራሉ፡፡ ነገር ግን መጨረሻቸው ጥፋት ስለሆነ ልናውቅባቸው ይገባል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተክርስቲያን አባቶች ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት የሐዋርያት የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ሁላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

 

 

 

© Copyright 1997 -2020. All rights reserved.