ነገረ ትንሣኤ
በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ
ጌታችን የሞተው በሥጋው ወይስ በመለኮቱ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጌታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት ‹‹እንደ ቃልህ ይኹንልኝ›› ባለችው ጊዜ መለኮትና ትስብእት ሁለትነትን አጥፍተው በአካልና በባሕርይ ተዋሐዱ፡፡ መለኮት ባሕርያዊ ታላቅነቱን ሳይለቅ በየጥቂቱ ማደግን ከሥጋ ገንዘብ አደረገ፤ ሥጋም ባሕርያዊ ታናሽነቱን ሳይለቅ ከሦስቱ አካላት እንደ አንዱ ኾነ (ዘፍ. ፫፥፳፪)፡፡ ይህ ተዋሕዶ አንዱን ለአንዱ ያስገዛ ተዋሕዶ ነው፤ መራብ፣ መጠማት፣ ሞት፣ ድህነትና እነዚህን የመሳሰሉት ዂሉ ያለ ተዋሕዶ ለመለኮት ሊስማሙ አይችሉም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ባለጠግነት፣ ሕይወት፣ ዘለዓለማዊት መንግሥት፣ የማነ አብ፣ ዘባነ ኪሩብና እነዚህን የመሳሰሉት ዂሉ ለሥጋ ይነገሩ ዘንድ የሚገባቸው አልነበሩም፤ ተዋሕዶ ምክንያት ኾኖ የመለኮትን ለሥጋ የሥጋን ለመለኮት ሰጥተን እንድንናገር አድርጎናል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም በድርሳኑ ‹‹እንቲአሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል፤ ወእንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ፤ የሥጋ ገንዘብ ለቃል የቃልም ገንዘብ ለሥጋ ኾነ›› ብሎ መናገሩም ይህንን የተዋሕዶ ፍጹምነት ለመግለጥ ነው፡፡
ሊቁ ይህን ምሥጢር ለማስረዳት የተጠቀመበት ምሳሌ የብረትና የእሳት ተዋሕዶ ነው፤ ብረት ሠሪ ብረቱን ከእሳት ሲጨምረው ብረቱ የእሳትን ባሕርይ ገንዘብ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጊዜ መልኩና ውዕየቱ የእሳት፤ ቅርፅና መጠኑ ደግሞ የብረት ይኾናል፡፡ ብረት ሠሪው በመዶሻ ብረቱን ሲቀጠቅጠው ሊያዝ የማይችለው እሳት ከብረት ጋር ተዋሕዶ ሲቀጠቀጥ እናያለን፡፡ ከብረቱ ጋር እሳት ባይዋሐድ ኖሮ ብረቱን ማስተካከል አይቻልም ነበር፡፡ መለኮት ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜም ሊይዙት ሊጨብጡት የማይቻል እሳተ መለኮት ተይዞ ተደበደበ፡፡ መለኮት በሥጋ መከራ ባይቀበል ኖሮ የሰው ባሕርይ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ እንደ ምን ይችል ነበር? ኀጢአት ያቀዘቀዘውን ባሕርያችንን ያስተካከለው መለኮት በሥጋ የተቀበለው መከራ ነው፡፡ እንደዚያማ ባይኾን ኖሮ ከአቤል ጀምሮ በግፍ የተገደሉ ብዙ ቅዱሳን መከራቸው ለምን አላስታረቀንም? የዕሩቅ ብእሲ ደም ሰውን ከኀጢአት ሊያነጻው ባለ መቻሉ ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን በገለጸበት ቅዳሴው ‹‹ኦ አእዳው እለ ለኃኳሁ ለአዳም ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል ኦ አእጋር እለ አንሶሰዋ ውስተ ገነት ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል ኦ አፍ ዘነፍሐ ውስተ ገጹ ለአዳም መንፈሰ ሕይወት ሰረበ ብሒአ፤ አዳምን የሠሩ እጆች በቀኖት ተቸነከሩ፤ በገነት የተመላለሱ እግሮች በቀኖት ተቸነከሩ፤ በአዳም ላይ የሕይወት እስትንፋስን እፍ ያለ አፍ መራራ ሐሞትን ጠጣ›› በማለት ያደንቃል፡፡ አዳምን የሠሩ የመለኮት እጆች ወይስ የትስብእት? በገነት ሲመላለሱ አዳም የሰማቸው እግሮች የመለኮት ወይስ የትስብእት? በአዳምስ ላይ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ብሎ ልጅነትን ያሳደረበት ማን ነው? ሥጋ ነው እንዳንል ሊቁ እየተናገረ ያለው ቅድመ ተዋሕዶ ስለ ተፈጸመ ታሪክ ነው፤ መለኮት ነው እንዳይባል የመለኮት እጅና እግር በችንካር የሚመታ፣ አፉም እንኳን መራራውን ጣፋጩን ሊጠጣ የማይችል ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ የሊቁ ቃል ይመልሰንና መለኮት በሥጋ መከራን እንደ ተቀበለ ያስረዳናል፡፡ እንደ ሰውነቱ ‹‹ተቸነከረ፤ መራራ ጠጣ›› እንላለን፡፡ እንደ አምላክነቱ ደግሞ የአዳም ፈጣሪ እንደ ኾነ እንናገራለን፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የተናገረው ቃል ቀዳማዊው ደኃራዊ፣ ደኃራዊው ቀዳማዊ መኾኑን የምንረዳበት አንቀጽ ነው፡፡ በጥንተ ፍጥረት ያልነበረ ሥጋ ፈጣሪነትን በተዋሕዶ ገንዘብ አድርጓል፡፡ ዓለምን የሠሩ መለኮታዊ እጆችም በሥጋ መከራን ተቀብለዋል፡፡ ስለዚህ የቀራንዮው መስቀል መለኮት ከትስብእት፣ ተስብእት ከመለኮት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመኾኑ የተቀበለው እንጂ ለሥጋ ብቻ የሚሰጥ አይደለም፡፡ መከራ የተቀበለው መለኮት ለብቻው ቢኾን ኖሮ አይሁድ እንዴት አድርገው መስቀል ያሸክሙታል? በገጸ መለኮቱ ፊት ቆመው እንደ ምን ይሳለቁበታል? በብርሃን የተከበበ ፊቱን መላእክት፣ ሐዋርያት ስንኳን ሊያዩት አይቻላቸውምና (ማቴ. ፲፯፥፩-፱)፡፡ ለመለኮትስ መሥዋዕት በሚኾን ገንዘብ ሥጋና ደም አለውን? መለኮት ለብቻው ቢሰቀል ኖሮ ደም እንዴት ይፈሳል? ሥጋስ ከየት መጥቶ ‹‹እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው›› ልንባል እንችላለን? (ዕብ. ፲፥፩-፲፱)፡፡
ሞት በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም እንደ ገባ፣ ሞትን የሚገድል ሞት ደግሞ በሁለተኛው አዳም በክርስቶስ በኩል ኾነ፡፡ መለኮት በሥጋው የሞተው ሞት እንጅ ሞትን የገደለው የዕሩቅ ብእሲ ሞት ብቻ አይደለም፡፡ የዕሩቅ ብእሲ ደም እንዴት ሥርየትን ሊሰጠን ይችላል? የዕሩቅ ብእሲ ሥጋስ እንዴት «ወሀቤ ሕይወት» ሊኾን ይችላል? ሞትን ያመጣ ሥጋ ዛሬ ግን ሕይወትን ለሙታን የሚያድል የሕይወት ምንጭ ኾነ (ዮሐ. ፬፥፲)፡፡ ዂሉን ይዞ የሞተው የአዳም ሥጋ ዛሬ ለዂሉ ሕይወትን ሰጠ፤ መቃብር የገዛው ባሕርያችን ዛሬ ዂሉን ከእግሩ በታች አድርጎ ገዛ፡፡ ለዚህ ዂሉ ምክንያቱ ምሥጢረ ተዋሕዶ ነው፡፡ ስለዚህ መለኮት በሥጋ ሞተ፤ ሥጋም በመለኮት ሕያው ኾነ ብለን እንናገራለን፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ሞተ በሥጋ ወሐይወ በመንፈስ፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ኾነ›› ብሎ መናገሩም ለዚህ ምስክር ነው (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፰)፡፡ መልክአ ኢየሱስም ‹‹ሰላም ለበድነ ሥጋከ እመለኮቱ ዘኢተፈልጠ ለሰዓት አሐቲ ከመ ቅፅበተ ዐይን ኅዳጠ፤ ለዐይን ጥቅሻ ለምታክል ሰዓት ስንኳን ከመለኮቱ ያልተለየ በድነ ሥጋህን ሰላም እላለሁ›› ይላል፡፡
በዕለተ ዓርብ መስቀል ላይ የዋለው የክርስቶስ ሥጋ ከመለኮቱ አልተለየም፡፡ በእርግጥ የሥጋ ሕይወት ነፍስ ተለይታዋለችና ሥጋው ‹‹ምውት›› ወይም ‹‹በድን›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሆኖም ጌታችን በመለኮታዊ ባሕርዩ ሞት አያሰጋውም፤ አይስማማውም፡፡ ስለዚህም ሕያው ሥጋ ነው፡፡ ሕያው መኾኑንም ከሞተ በኋላ ለንጊኖስ በጦር በወጋው ጊዜ ደምና ውኃ ከጎኑ በመፍሰሱ እናረጋግጣለን፡፡ ከሞተ ሰው ደም ይወጣ ዘንድ የተፈጥሮ ሕግ አይደለምና፡፡ ምውትነቱን ደግሞ ‹‹አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ›› ብሎ በፈቃዱ ነፍሱን በመስጠቱ እናረጋግጣለን፡፡ በአጠቃላይ ቃል፣ ሥጋ መኾንን የወደደው የሥጋን ድካም ለማገዝና በሥጋ ድካም ጠንካራውን ጠላት ዲያብሎስን ለማሸነፍ ነው፡፡ በመኾኑም በአራት ዓለማት ውስጥ በሰው ላይ ይደርሱ የነበሩ ችግሮቹን በአካል ተገኝቶ አስወግዶለታል፤ እነዚህም ማኅፀነ አንስት፣ ምድር፣ መቃብርና ሲኦል ናቸው፡፡
መርከስ እንጀምርበት በነበረው ማኅፀን መቀደስን እንደ ጀመርን ማረጋገጫ ይኾነን ዘንድ በእመቤታችን ማኅፀን የመላእክት ቅዳሴ ይሰማ ነበር፡፡ የሴት ማኅፀን ርኵሰት የሚጀመርበት የሰው ልጆች ዓለም ነበረ፤ ዛሬ (ጌታችን ሲወለድ) ግን «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ» ተብሎ የሚመሰገንበት ቦታ ኾነ፡፡ ሴቶች ከወለዷቸው ዂሉ ሕዝቡን ከኀጢአት ሊያድናቸው የተቻለው ማንም አልነበረም፤ ዛሬ ግን ከኃጢአት ንጹሕ ኾኖ ኃጢአትን የሚያርቅ ጌታ ተገኝቶበታል፡፡ ርኵሰታችን ከሚጀምርበት ከማኅፀን ጀምሮ የርኵሰታችን ዋጋ እስከ ኾነችው ሲኦል ድረስ በሔድንበት ሒዶ ችግራችንን አስወገደልን፡፡ ይህን ሲያደርግ ግን መለኮት ከሥጋ የተለየበት አንዳች እንኳን ጊዜ እንደ ሌለ እናምናለን፡፡
«ተራብሁ» (ሉቃ. ፬፥፪) ብሎ መናገር የሚስማማው ለሥጋ ብቻ ቢኾንም፣ መለኮትም በሥጋ እንደ ተራበ እንናገራለን፡፡ ኅብስት አበርክቶ መመገብ የሚቻለው ለባለ ጠጋው መለኮት ቢኾንም ለሥጋም ተገብቶታል፡፡ ጌታችን፣ ሣምራዊቷ ሴት ውኃ በከለከለችው ጊዜ ‹‹የሚለምንሽ ማን እንደ ኾነ ብታውቂስ ኖሮ አንች በለመንሽው፣ እርሱም ደግሞ የሕይወትን ውኃ በሰጠሽ ነበር›› ሲል የሰማነው በሥጋው ነው፡፡ ለራሱ የሌለው ሥጋ ለሌላው መስጠት ጀምሯልና፡፡ ሞትንም ስናነሣ ለሥጋ ብቻ ሳይኾን መለኮትም በሥጋ እንደ ሞተ፤ መለኮትም በሥጋ በመቃብር እንዳደረ እንናገራለን፡፡ ይህን የምንናገረው ግን እርሱ ሞቶ ለሙታን ሕይወትን የሚሰጥ መኾኑን ሳንረሳ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሊቁ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹ውእቱ ውስተ መቃብር ወያነሥእ ሙታነ፤ እርሱ በመቃብር ያደረ ሲኾን ሙታንን ያስነሣል›› ሲል የሚናገረው (ሃይማኖተ አበው፣ ፲፩፥፬)፡፡
ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት
ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሲገንዙት ጌታችን ‹‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት› … እያላችሁ ገንዙኝ›› ብሏቸዋል፡፡ ይህ ቃል አንደኛ ጌታችን የቀደመውን መርገም እንደ ሻረው የተረዳንበት ነው፡፡ በዘመነ ኦሪት የሞተ ሰው ብቻ ሳይሆን በድኑን የነካውም ርኩስ ነበር፡፡ ይህ ልማድ ለመሻሩ ማረጋገጫችን “ቅዱስ እግዚአብሔር” የሚለው ቃል ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሞት አንዱ የሕይወት መንገድ እንጂ ለሲኦል እና ለመቃብር የሚያሰጥ ፍርድ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ጌታችን መለኮታዊ ባሕርይው የተለየው መስሏቸው እንደ ነበር ያስረዳናል፡፡ በግዕ ነባቢ የተባለው ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ለዘመናት አበው ያቀረቡትን የሕይወት ጥያቄ ለመመለስ ነው፡፡ ዮሴፍና ኒቆዲሞስም ፈጽሞ ሕይወት እንደ ተለየው በማሰብ ይገንዙት ነበርና ይህን ጥያቄአቸውን ለመመለስ በቃሉ አናግሯቸዋል፡፡ በሥጋ ቢሞት በመንፈስ ግን ሕያው ነውና፡፡
ሦስተኛ ኃጢአትን የሚያስተሠርይ እውነተኛ መሥዋዕት መኾኑን ለማስገንዘብ የተነገረ ቃል ነው፡፡ እስካሁን የቀረቡት መሥዋዕቶች ዂሉ ሞት የገዛቸው ነበሩ፡፡ ክርስቶስ ግን ከሞት አገዛዝ ውጪ በመኾኑ ከሞተ በኋላ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር በሉኝ›› ብሎ ተናግሯል፡፡ ‹‹ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት›› እንዲሉት መናገሩም በሥጋው ቢሞት በመለኮቱ ግን ሕያው መኾኑን ለማስረዳት ነው፡፡ አራተኛ ባሕርየ መለኮቱ በሥጋው መከራ እንደ ተሳተፈ ለማሳወቅ ነው፡፡ መለኮት የሥጋን ውርደት፣ ሥጋም የመለኮትን ክብር ካልተሳተፈ የተዋሕዶ መገለጫው ምን ሊኾን ይችላል? ያለ ሥጋ እንዴት ኾኖ በድርብ በፍታ፣ በተልባ እግር ልብስ ሊሸፈን ይችላል? ያለ መለኮትስ ከሞት በኋላ እንዴት ሊናገር ይችላል? የሥጋ ሕይወት ነፍስ ናትና፡፡
የሙታን ሕይወታቸው፣ በመቃብር ላሉት ትንሣኤያቸው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና መቃብር ሊወስነው አይችልም፡፡ ደቀ መዛሙርቱን ሳይቀር ‹‹ሙታንን አንሡ›› ብሎ ሥልጣንን የሰጠ ጌታ እንዴት በሞት ግዛት ውስጥ ሊወሰን ይችላል? አይደለም! ‹‹በመቃብር አደረ›› እንላለን እንጅ ‹‹መቃብር ወሰነው›› አንልም፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹ውእቱ ውስተ መቃብር›› ካለ በኋላ ‹‹ውእቱ አፍኣ እመቃብር፤ እርሱ ከመቃብር ውጭም አለ›› ብሏል፡፡ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በድርብ በፍታ ሲገንዙት በሰማይ ደግሞ በባሕርይ ክብሩ ጸንቶ አለ፡፡ በምድር መከራ በሚያጸኑበት አይሁድ ፊት መከራን ይቀበላል፤ በሰማይ ደግሞ ከመላእክት ምስጋና ይቀርብለታል፡፡
እነዚህ ዂሉ መለኮት በሥጋ መሞቱንና መከራ መቀበሉን፤ ሥጋም በመለኮት ሕይወት፣ መድኃኒት መባሉን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ እንዲህ ስንል ግን ‹‹መለኮት ሞተ›› እንዳንል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹በሥጋው ሞተ›› ትላለች እንጂ ‹‹በመለኮቱ ሞተ›› አትልም፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹ለእመ ትቤ መለኮት ሞተ አንተ ቀታሊሆሙ ለአብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ መለኮት ሞተ የምትል ከኾነ የአብ የመንፈስ ቅዱስ ገዳይ አንተ ነህ›› ብሏል (ሃይ. አበ. ፲፩፥፲፫)፡፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በባሕርይ አንድ ናቸውና፡፡ ስለዚህ ‹‹መለኮት በሥጋ ሞተ፤ ሥጋ በመለኮት ሕያው ኾነ›› የሃይማኖታችን ትምህርት ነው፡፡
ጌታችን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ስለ መነሣቱ
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞቱ አስቀድሞ ‹‹ነፍሴን ላኖራትም፣ ላነሣትም ሥልጣን አለኝ›› በማለት ተናግሯል (ዮሐ. ፲፥፲፯-፲፰)፡፡ በሐዋርያት ሥራ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው›› ተብሎ ተጽፏል (ሐዋ. ፪፥፲፭-፳፮)፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹ጌታችን ከሙታን የተነሣው በራሱ ሥልጣን አይደለምን? እነዚህ ኃይለ ቃላትስ አይጋጩምን?›› የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ወደ ምላሹ ስንመጣ ነገረ ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት ዓይነት አንድምታ አለው፡፡ ሐዋርያት ስለ እርሱ በጻፉት በሰበኩት ቃል ዂሉ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ መኾኑን ለማስረዳት አንዳንድ ጊዜ ፍጹም ሰው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፍጹም አምላክ ሲያደርጉት እንመለከታለን፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ‹‹የሚያበረታው መልአክ መጣ፤ ከብርቱ ጩኸትና ልመና ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ጸሎቱ ተሰማለት›› (ዕብ. ፭፥፯) በማለት ጌታችንን ከአዳም ልጆች እንደ አንዱ በማስመሰል ደካማ ቃላትን ተናግሮለታል፡፡ በዚህም አምላካችን ክርስቶስ ድካማችንን ለማገዝ መድከሙን እንረዳበታለን፡፡ ኀይለኛውን ጠላታችንን አስሮ፣ ሲኦልን በርብሮ ነፍሳትን ነጻ እስኪያወጣ ድረስ ጌታችን ደክሞ ታይቷልና ደካማ ቃላት ተነገሩለት፡፡ ለመለኮትማ ከአንዱ ወደ አንዱ ይሔድ ዘንድ ጎዳና አለበት እንዴ? በእውነት ስለ ሥጋ ድካም ይህ ዂሉ ተባለ፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍትም ሰው መኾኑን እንደ ነገሩን ዂሉ ፍጹም አምላክ መኾኑንም ሲመሰክሩ ‹‹ተኀድገ ለከ ኃጢአትከ፤ ፈቀድኩ ንጻሕ፤ ኀጢአትህ ተደመሰሰልህ፤ ፈቅጃለሁ፥ ንጻ›› እያለ በሥልጣኑ ኀጢአተኞችን ከበደል ነጻ እንደሚያደርግና ሕሙማንን እንደሚፈውስ ነግረውናል፡፡ ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ይህን ያደርግ ዘንድ ሥልጣን ያለው የለምና፡፡ በዚያውም ላይ ነፋሳትን ሲገሥፅ፣ አጋንንትን ሲያስደነግጥ ዐይተን፤ እንደ አምላክ ባለ ሟሎች በእግዚአብሔር ስም ሳይኾን በራሱ ስም ተአምራትን ሲያደርግ ስንመለከተው አምላክ መኾኑን አወቅን፡፡ ስም አጠራሩን ስንመለከት አንዳንድ ጊዜ ‹‹ወልደ ዳዊት››፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹ወልደ እግዚአብሔር›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ‹‹ወልደ ዳዊት›› በመባሉ ምድራዊ ልደቱን፣ ‹‹ወልደ እግዚአብሔር›› በመባሉ ደግሞ ሰማያዊ ልደቱን ተረዳን፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ‹‹ወልደ ዳዊት›› እየተባለ የመጠራቱ ምሥጢርም እኛ ሰማያውያን እንሆን ዘንድ እሱ ምድራዊ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ክርስቶስ ሲነገር ማንኛውም ምእመን የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ሊል ይገባል፤
፩ኛ ለካሣ የተነገሩ ቃላት መኖራቸውን
በቅዱስ ወንጌል ‹‹አባቴ ላከኝ፤ ይህን ሥልጣን ከአባቴ ተቀብያለሁ›› የሚሉ ቃላት በተደጋጋሚ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ ያ ማለት ግን ምድራዊ አባት በልጁ፣ ልጅም ለአባቱ እንደሚያደርገው በአብ እና በወልድ መካከል ማዘዝ፣ መታዘዝ፣ መላክ፣ መላላክ ኖሮ አይደለም፡፡ ‹‹ኢይኤዝዞ አብ ለወልዱ በከዊነ አብ ወኢየዐቢ ወልድ በከዊነ ወልድ፤ አብ ልጁን አባት በመሆን አያዝዘውም፤ ወልድም ልጅ በመሆኑ እንቢ አይልም›› እንዳለ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡ ታዲያ ለምን እንዲህ ይላል ያሉ እንደ ኾነ ቀዳማዊ አዳም ባለ መታዘዙ የመጣበት መከራ፣ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ እስከ መስቀል ድረስ ባደረገው መታዘዝ እንደ ተወገደለት ለማስረዳትና የአዳምን አለመታዘዝ በመታዘዝ ለመካሥ ነው፡፡
፪ኛ ጌታችን ፍጹም ሰው መኾኑን ለማስረዳት የተነገሩ ቃላት መኖራቸውን
ጌታችን ‹‹ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች›› ሲል ኀዘን የሚስማማው ሰውነትን እንደ ተዋሐደ ለማስረዳት ነው፡፡ ‹‹… ዋጋችሁ ብዙ ነውና ደስ ይበላችሁ›› እያለ የምሥራችን የሚሰብክ ጌታ እንዴት አዘነ ተብሎ ይነገርለታል?
፫ኛ የጠፉትን ለመፈለግ የተነገሩ ቃላት መኖራቸውን
ጌታ ‹‹አንቺ ሆይ፥ ውኃ አጠጭኝ›› ማለቱ ለሣምራዊቷ ሴት የሕይወትን ውኃ ለማጠጣት እንጂ እርሱ ውኃ ስለ ጠማው የተናገረው አይደለም፡፡ እንዲያማ ቢኾን ኖሮ በኋላ ውኃ ሲጠጣ ባየነው ነበር! ከዚያ ይልቅ ለሴቲቱ የሕይወትን ውኃ አጠጥቶ መሔዱን ስንመለከት ቃሉ የጠፋችውን ሴት ለመፈለግ የተነገረ መኾኑን እንረዳለን፡፡ ከላይ የተነሣው ጥያቄም ከእነዚህ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ለመነሣት እንደ አልዓዛር፣ እንደ ወልደ መበለት ድምፅ የሚያሰማውና ከመቃብሩ በር ላይ ተንበርክኮ የሚጸልይለት ጻድቅ አያስፈልገውም፡፡ በገዛ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል እንጂ፡፡ ለዚህም ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ›› ማለቱን ልብ ይሏል (ዮሐ. ፪፥፲፱)፡፡ በዚህም ሰውነቱን ከሞት እንደሚያነሣው ሥልጣን እንዳለው አሳይቶናል፡፡
በመሠረቱ ‹‹እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው›› (ሐዋ. ፪፥፲፭-፳፮) የሚለው ኃይለ ቃል፣ እግዚአብሔር እንዳስነሣው እንጂ አብ እንዳስነሣው የሚናገር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በሚለው ስም አብ ብቻ ሳይኾን ወልድና መንፈስ ቅዱስም ይጠሩበታል፡፡ አባቶቻችን የዚህን ኃይለ ቃል ምሥጢር ሲያስረዱ ‹‹እግዚአብሔርነቱ አስነሣው›› ብለው ይተረጕሙታል፡፡ ይኸውም ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ስም ባሕርያዊ ስም እንጂ አካላዊ ስም ስላልኾነ ነው፡፡
አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔር አምላክህ ቀባህ … እግዚአብሔርም የናዝሬቱን ኢየሱስን በኃይልና በመንፈስ ቀባው … እግዚአብሔርም ከሙታን መካከል ለይቶ አስነሣው …›› ሲል ሲሰሙ የእምነት መሠረታቸው ይናወጥባቸዋል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ በመጽሐፈ ምሳሌ ፰፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል ሲተረጕም ‹‹ጥበብ ‹ጌታ ፈጠረኝ› አለች እንጂ ‹አብ ፈጠረኝ› አላለችም፤ ወልድ ስለ አባቱ መናገር በፈለገ ጊዜ ‹አባቴ› ብሎ ለይቶ የሚናገር አይደለምን?›› በማለት ለአርዮሳውያን የሰጠውን ምላሽ መመልከቱ ለዚህ ይጠቅማል (ሃይ. አበ. ፸፮፥፲፫)፡፡ ስለዚህ ‹‹አብ አነሣው›› ብለው ለሚሳሳቱ፣ ለሚያሳስቱ ወልድ በሥልጣኑ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ መኾኑን እንነግራቸዋለን፡፡
ሴቶች የጌታችንን ትንሣኤ የማየታቸው ምሥጢር
ቅዱስ ጳውሎስ ሴቶች በማኅበር መካከል መናገርና ማስተማር እንደማይገባቸው ተናግሯል (፩ኛ ቆሮ. ፲፬፥፴፭)፡፡ አንዳዶቹ ጌታችን ወደ መቃብሩ የሔዱትን ሴቶች ‹‹ወደ ገሊላ እንዲሔዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ›› ማለቱን በመጥቀስ ሴቶች ወንጌል ማስተማር ይችላሉ የሚል መከራከሪያ ያነሣሉ (ማቴ. ፳፰፥፩-፲)፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ለቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት የቀናን ይመስላቸውና ሲሳሳቱ እናያቸዋለን፡፡ የሴቶችን አለመስበክ ሲያስተዉሉ፣ ሴቶች የማይገቡባቸው ገዳማትን ሲያዩ እንደ መብት ጥሰት የሚቈጥሩት አሉ፡፡ አዳም ጥንት ሲፈጠር ያለ ሴት ብቻውን ለአንድ ሱባዔ ቆይቷል፡፡ ሴት የማይገባባቸው ገዳማት መኖራቸው ከሔዋን መገለጥ በፊት የነበረውን አዳም ለመግለጥ እንደ ሆነ መረዳት ይገባል፡፡
ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን መሰብሰብ ሲጀምር ሠላሳ ስድስቱን ሴቶች እንዲኾኑ ማድረጉ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሴቶች ለወንጌል አገልግሎት መጠራታቸውን ልናምን ይገባናል፡፡ ከተጠሩት ቅዱሳት አንስት መካከልም ወንጌልን ሰብከው ብዙዎችን ወደ ማመን እንደ መለሷቸውና እንዳስጠመቋቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ እንዲህ ስላልን ግን በጉባኤ ወጥተው ያስተምሩ ነበር ማለታችን አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የከለከለውም ይህንኑ ነው፡፡ በእርግጥ ሴቶች፣ ሴቶችን ሰብስበው ያስተምሩ ነበር፡፡
ለማርያም መግደላዊት መጀመሪያ ትንሣኤውን የገለጠውና ‹‹ሒደሽ ለወንድሞቼ ንገሪያቸው›› ብሎ የላካት ለምንድን ነው? ከተባለ ሞት ወደ ዓለም ሲገባ የተሰበከው በሴት አንደበት ነበር፤ በሴት እጅ በተቈረጠ ዕፀ በለስ፣ በሴት አንደበት በተሰበከ ስብከት ሞት ወረሰን፡፡ በዚህም ምክንያት ሴቶቹ ርስት አይካፈሉም፤ ከቍጥር ገብተው አይቈጠሩም ነበር፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም ችግሮች በእርሱ ቤዛነት እንዳስቀረላቸው ለማጠየቅ ጌታችን ለሴቶች ተገለጠ፡፡ ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ሴት፣ ሞትን በሰበከችበት አንደበቷ ትንሣኤውን እንድትነግር፤ ወደ ዕፀ በለስ በሮጠችባቸው እግሮቿ ወደ ሐዋርያት እንድትገሰግስ አደረገ፡፡ በዚያውም ላይ ቀዳማዊ አዳም ከእንቅልፉ ሲነቃ ከጎኑ ያገኛት ሔዋንን ነበር፡፡ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ከሞት በተነሣ ጊዜ ከመቃብሩ በአፍኣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች ተገኝተዋል፡፡
በዓለ ትንሣኤ፣ ‹ፋሲካ› እየተባለ የሚጠራበት ምክንያት
የፋሲካ በዓል በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ፓሳህ› ይባላል፤ ትርጕሙም ‹ማለፍ› ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለ ትንሣኤ አንደኛ ሞት፣ ከእስራኤል መንደር ያለፈበት ስለ ኾነ ነው፤ ግብፅ በረሃብ እንዳትመታ ፈርዖናቸው ያደረገው ነገር ባይኖርም መጻተኛውና ወደ ወኅኒ የወረደው ዮሴፍ ግን የረሃብ ሞትን ወደ ግብፅ እንዳይገባ ከለከለው፡፡ ዳሩ ግን ዮሴፍ ሲያልፍ የዮሴፍን ታሪክ የማያውቅ ሌላ ፈርዖን ተሾመና በእስራኤል ላይ የሞት ሕግ አወጣ (ዘፀ. ፩፥፲፩)፡፡
‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፡፡ እርሱ ራስ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኰና ሰኰናውን ትነድፋለህ›› (ዘፍ. ፫፥፲፭) ተብሎ የተነገረለት ዲያብሎስ ራስ ራሱን የሚቀጠቅጥ ወንድ እንዳይወለድ በማሰቡ ሕፃናትን ከማኅፀን እያስቀረ፤ ለመቃብርም እያቀበለ እስከ ሙሴ ዘመን ደረሰ፡፡ ከሙሴ መምጣት በኋላ ሞት የእስራኤልን መንደር ለቅቆ ወደ ግብፃውያን መንደር እንዲገባ ምክንያት የኾነው ዕለትም ፋሲካ ይባላል፡፡ በዚህ በዓል ላይ እስራኤላውያን የበግ ጠቦት አርደው የቤታቸውን ጉበን የቀቡትን ደም የተመለከተው ሞት እነርሱን ትቶ የግብፃውያንን የበኵር ልጆች ገደለ፡፡ እስራኤላውያን ‹‹ቀሣፊያችን ተቀሠፈ›› ሲሉ በዓላቸውን ‹ፋሲካ› አሉት፡፡
እኛም በሐዲስ ኪዳን የጌታችንን ትንሣኤ ፋሲካ የምንለው ሞት ከእኛ ያለፈበት የመጀመሪያው በዓላችን በመሆኑ ነው፡፡ ስለ ብዙዎች ይቅርታ የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም በግብፅ ከተሠዋው በግ ይልቅ የከበረ መሥዋዕት ነውና ያሉትን ከማዳኑም ባሻገር የሞቱትንም ከመቃብር አውጥቷል፡፡ በእርሱ ትንሣኤ ሞት ከእኛ ማለፉንና የሰው ባሕርይ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱንም ‹‹ለምንት ተኀሥሣሁ ለሕያው ምስለ ምዉታን፤ ሕያዉን ከሙታን ጋር ስለ ምን ትፈልጉታላችሁ›› ከሚለው ኃይለ ቃል እንረዳለን (ማቴ. ፳፰፥፮)፡፡ ምዉታን ያላቸውም አጋንንት ናቸው፡፡ በጌታችን ትንሣኤ ሰው ከሙታነ ሕሊና ከአጋንንት ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ ‹‹ኦ! አዳም መሬት አንተ ወትገብዕ ውስተ መሬት፤ አዳም ሆይ ቀድሞም መሬት ነህ፤ ወደ መሬትነትህም ትመለሳለህ›› የሚለው አዋጅ አሁን ተቀይሯል፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ከሚያረጀው ወደማያረጀው፣ ከሚበሰብሰው ወደማይበሰብሰው ሰውነት የተሸጋገርንበት በዓል ነው፡፡ ይህ ዂሉ መሸጋገር የተፈጸመው በፋሲካው በግ ምክንያት በመኾኑ ክርስቶስን ፋሲካችን እንለዋለን (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፯)፡፡
ሁለተኛ ‹‹መሥዋዕተ ኦሪት አለፈ፤ መሥዋዕተ ወንጌል ደረሰ›› የምንልበት ወቅት ስለ ኾነ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለደቀ መዛሙርቱ በሰጠበት ዕለት በፋሲካ የተጀመረችውን ሕግ በፋሲካ ይሽራት ዘንድ የሚያልፈውን መሥዋዕተ ኦሪት አስቀድሞ፣ የሚመጣውን መሥዋዕተ ወንጌል አስከትሎ ፋሲካን አደረገ፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ‹‹ዝ ውእቱ ደምየ ዘይትከአው ለሐዲስ ሥርዓት በእንተ ቤዛ ብዙኃን፤ ስለ ብዙዎች ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው›› (ማቴ. ፳፮፥፳፰) በማለት ወደ ሐዲስ ኪዳን መግባታቸውን አስረግጦ ነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ትንሣኤ አሮጌውን ትተን ወደ አዲስ ሕይወት የተሸጋገርንበት በዓል በመኾኑ ፋሲካ እንለዋለን፡፡
ሦስተኛ የደስታችን ማረጋገጫ ስለ ኾነ ነው፡፡ ‹ፋሲካ› ማለት በግእዝ ቋንቋ ‹ደስታ› ማለት ነው፡፡ ደስታችን የተረጋገጠው በጌታችን ትንሣኤ ሲኾን ፍጻሜውን የሚያገኘው ደግሞ በትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጌታችን በዕለተ ዓርብ በቈረሰው ቅዱስ ሥጋውና ባፈሰሰው ክቡር ደሙ ተመሥርታለች፡፡ ምንም እንኳን በሕዝብና በአሕዛብ ፊት ደስታዋን የምትገልጥበት ጊዜ ገና ቢኾንም፣ በትንሣኤው ግን በዝግ ቤት ውስጥ ኾና የክርስቶስን ሰላምታ ተቀብላ ተደስታለች (ዮሐ. ፳፥፲፱)፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፤ ተኀፂባ በደመ ክርስቶስ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ደስ ትሰኛለች›› እያልን የምንዘምረው፡፡
ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስቶስ የትንሣኤዋ በኵር ኾኖ ተነሥቶላታልና ሊገድሏት በሚጎትቷት ሰዎች ፊት ለሽልማት እንደ ተጠራ ብላቴና ደስ እያላት ትቀርባለች (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፳)፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደስታዋን በትንሣኤ ፍጹም እንደምታደርገውም ቅዱስ አርክዎስ በሃይማኖተ አበው ፱፥፩ ላይ ‹‹በዛቲ ዕለት ተፈጸመ ፍሥሐሃ ለቤተ ክርስቲያን፤ በዚች ቀን የቤተ ክርስቲያን ደስታ ፍጹም ኾነ›› በማለት ይመሰክርላታል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የጌታችን ትንሣኤ ፋሲካ ተብሎ ይጠራል፡፡
ጌታችን በኵረ ትንሣኤ የተባለበት ምክንያት
የመጀመሪያው አዳም ለሞትና ለኀጢአት በኵር ሆኖ ነበርና ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ ሞት ሲገዛን ኖሯል (ሮሜ. ፭፥፲)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ክርስቶስ ላንቀላፉት (ለሙታን) በኵራት ኾኖ ከሙታን ተነሥቶአል” በማለት ጌታችን የትንሣኤያችን በኵር መኾኑን ነግሮናል (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፳)፡፡ ከጌታችን በፊት የሞቱና ከሙታን የተነሡ አሉ፡፡ ነገር ግን የጌታችን ትንሣኤ ከሌሎች ትንሣኤ የተለየ ነውና በኵረ ትንሣኤ (የትንሣኤ መጀመሪያ) ይባላል፡፡ ጌታችን በኵረ ትንሣኤ መባሉም፡-
አንደኛ ሞቱ፣ ሞትን ስላጠፋ ነው፡፡ የጌታችን ሞት ከሌሎች ሙታን የተለየ ነው፡፡ ሞትን በመግደል ድሩን ሳይኾን የችግሩን ምንጭ ሸረሪቱን አጥፍቶታል፡፡ ኀጢአት፣ ሞት፣ መቃብር እነዚህ ሦስቱ ተያያዥ ነገሮች ናቸው፡፡ ኀጢአት ከሌለ ሞት፣ ሞትም ከሌለ መቃብር አይኖርም፡፡ ሞት ሲሞት ሙታን ተነሡ፤ የሞት ጥላ ሲገፈፍ መቃብራት ተከፈቱ፡፡ በክርስቶስ ሞት ኀጢአት ከሥሯ እንደ ተነቀለች ዛፍ ላታፈራ፣ ላትለመልም ለዘለዓለም ተነቀለች፡፡ ሞትም ሙታንን ለቆ ጠፋ፤ መቃብርም ባዶ ኾኖ ተከፈተ፡፡ ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴዋ ‹‹ሞተ ዘቦአ ቀዳሚ ውስተ ዓለም በቅንዓተ ሰይጣን አብጠልከ በምጽአቱ ለዋሕድ ወልድከ መድኃኒነ፤ በሰይጣን ተንኮል ከልጅህ መምጣት አስቀድሞ ወደ ዓለም የገባ ሞትን በልጅህ ሰው መኾን አጠፋህ›› እያለች የምታመሰግነው (ሥርዓተ ቅዳሴ)፡፡
ጌታችን በኵረ ትንሣኤ የተባለበት ሁለተኛው ምክንያት የጌታችን ትንሣኤ የመጀመሪያው ሐዲስ ትንሣኤ ስለ ኾነ ነው፡፡ ከእርሱ በፊት ከሙታን የተነሡ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም በሚበሰብስ ሥጋ ተዘርቶ በማይበሰብስ ሥጋ መነሣት የቻለ ማንም አልነበረም፡፡ ሌሎቹ ሙታን ለዘለዓለም ሞትን ማሸነፍ በሚችል ሞት የተነሡ አልነበሩምና (፪ኛ ነገ. ፲፫፥፳፩)፡፡ ክርስቶስ ከመጣ በኋላ የተነሡት እንደነአልዓዛር ያሉትም ዳግመኛ መሞትና መነሣት አለባቸው፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ግን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ እኛም ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ እንደ መላእክት ኾነን እንኖራለን፡፡ በሚፈርስ፣ በሚበሰብስ ሥጋ ተዘርተን (ሞተን)፣ በማይፈርስ፣ በማይበሰብስ ሥጋ እንነሣለን፡፡ የትንሣኤያችን በኵር ክርስቶስ ነውና፡፡
ጌታችን በኵረ ትንሣኤ የተባለበት ሦስተኛው ምክንያት፣ ትንሣኤው ስለ ዂላችንም ቤዛ የተደረገ ትንሣኤ ስለ ኾነ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ስለ ዂላችን (ለዓለም) የሞተ የለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እስመ ኵሉ ፆሮ ይፀውር፤ ዂሉም የራሱን ሸክም ይሸከማል›› ብሎ እንደ ተናገረው (ገላ. ፮፥፭)፣ አባቶቻችን በራሳቸው ዕዳ ሲሞቱ ምንም ዕዳና በደል የሌለበት ክርስቶስ ግን ለፍጥረት ዂሉ ዕዳ ሊደመስስ በፈቃዱ ሞተ፡፡ ሞቱ ስለ ዂላችን እንደ ኾነ ዂሉ ትንሣኤውም የዂላችን ሕይወት ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነን የአይሁድ ፍርሃት ነው፡፡ አይሁድ ‹‹በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ማለቱን ሰምተናል፤ ደቀ መዛሙርቱ ሌሊት መጥተው እንዳይሰርቁት፣ ‹ተነሣም› ብለው ለሕዝብ እንዳያስተምሩ ...›› ነበር ያሉት (ማቴ. ፳፯፥፷፪-፷፭)፡፡
ይህ የአይሁድ ፍርሃት የዲያብሎስም ጭንቀት ነው፡፡ ጌታችን ክብርት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ሲለያት ዲያብሎስ ነፍሱን በሲኦል ውጦ፣ ሥጋውን በመቃብር ረግጦ ማስቀረት እንዳልተቻለው ስለ ተረዳ አይሁድን እንዲህ እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ትንሣኤውን ዐይተው ያምኑ ዘንድ ይህን ማለታቸው የጌታ ፈቃድ ነበር፡፡ አምነው ባይጠቀሙበትም የጌታ ትንሣኤ ላመኑትም ላላመኑትም ሕይወት ነውና፡፡ ስለዚህ ነው የጌታችንን ትንሣኤ በኵረ ትንሣኤያችን የምናደርገው፡፡
ትንሣኤ ዘጉባኤ
በእሳት ተቃጥለው፣ በአራዊት ተበልተው ወደ ዐመድነትና አፈርነት የተለወጡ ሰዎች፣ በዕለተ ምጽአት ከሞት የሚነሡት እንዴት ነው? እንደ ገና ሰው ኾነው ይፈጠራሉ ማለት ነው?
በመጀመሪያ ካለመኖር ወደ መኖር እንድንመጣ ያደረገን ጥበበ እግዚአብሔር ነው፡፡ ያለዚያማ እንዴት ኾኖ ነው ከአባት የተከፈለው ዘር ከሴት ደም ጋር ተዋሕዶ፣ ብጥብጥ የነበረው ረግቶ፣ የአጥንት ምሰሶ የጅማት ማገር ተሠርቶለት ቅዱስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚኾነው? በእርግጥ እንዲህ ኾኖ የተጀመረው ህልውናችን በሞት ሲቋረጥ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ በመቃብር ውስጥ ቀልጦ ለመቅረት እንጂ ተመልሶ ለመብቀል አልነበረም፡፡ የሰው ልጅ እንደ አዝርዕት ከሞተና ከፈረሰ በኋላ አካል ኖሮት የሚነሣ ነው፡፡ ያለ ዝናም የአዝርዕት ምን ትንሣኤ አላቸው? ያለ ክርስቶስ ደም መፍሰስስ የሰው ልጅ ማን ከሞት ሊያስነሣው ይችላል? የጌታችን ደም ሲፈስ ግን መቃብራት ተከፈቱ፤ ዐለቶች ተሰነጣጠቁ፤ ከሙታን ወገን ብዙዎቹ ተነሡ፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቦኑ ለከንቱ ፈጠርኮ ለኵሉ እጓለ እመሕያው፤ በውኑ ሰውን ዂሉ ለከንቱ ነገር ፈጥረኸዋልን?›› የሚለው የአባቶቻችን ጥያቄ ምላሽ አገኘ (መዝ. ፹፰፥፵፯)፡፡
ሞት እንደ ገበሬ፣ መቃብር ደግሞ እንደ እርሻ ኾኖ የሰው ልጆች በዚህ ምድር በመበስበስ በመፍረስ እንዘራለን፡፡ እንዲህ ካልኾንን ትንሣኤ የለንም፡፡ በኋላም ተለውጠን በአዲስ ሥጋ እንነሣለን፡፡ ባሕርይ መልአካዊ፣ ባሕርይ ሥጋዊ፣ ባሕርይ እንስሳዊ ለዂላችንም በተፈጥሮ ይሰጡናል፡፡ ስንሞት ባሕርይ እንስሳዊ እና ባሕርይ ሥጋዊ ይለዩናል፡፡ ባሕርይ መልአካዊ ግን በባሕርዩ ሞት ስለ ሌለበት አብሮን ይኖራል፡፡ በምንም ዓይነት ሞት ብንሞትም ይህ የማይቀር ጉዳይ ነው (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፴፭-፵፬)፡፡ ትንሣኤ፣ የሰው ልጅ ፍሬ ሠላሳ፣ ስልሳና መቶ ፍሬ አፍርቶ የሚታይበት ወቅት ነው፡፡
ዕፅዋትና አዝርዕት ከፈረሱ፣ ከበሰበሱ በኋላ አንዱ በራሱ፣ ሌላው በጎኑ፣ ሌላው በሥሩ ያፈራል፡፡ ከሥሩ የሚያፈራው የባለ ሠላሳ፣ ከጎኑ የሚያፈራው የባለ ስልሳ፣ ከራሱ የሚያፈራው የባለ መቶ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ዳግም ልደት›› ተብሎ ይጠራል፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮዎች ሁለት ዓይነት ሲኾኑ፣ እነዚህም ጥንተ ተፍጥሮና ሐዲስ ተፈጥሮ ይባላሉ፡፡ ጥንተ ተፈጥሯችን በአዳም በኩል የተደረገው ተፈጥሯችን ሲኾን፣ ሐዲስ ተፈጥሮ የምንለው ደግሞ በክርስቶስ በኩል የተደረገውን የባሕርያችንን መታደስ ነው፡፡ ልደታችን ግን ሦስት ወገን ነው፡፡ አንደኛው ሥጋዊ፣ ሁለተኛው መንፈሳዊ፣ ሦስተኛው ደግሞ ትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፡፡ ይህም “ልደተ ሙታን እመቃብር” ይባላል፡፡ ይኸውም የሙታን ከመቃብር መወለድ ማለት ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት ማለትም በትንሣኤ ዘጉባኤ ከሞት የምንነሣውም በዚህ መልኩ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡